አርባዕቱ እንስሳ
ኪሩቤል ሱራፌል የተባሉት የልዑል እግዚአብሔርን ዙፋን በፍርሀት በረዐድ ኹነው የሚሸከሙ መላእክት ሲኾኑ ነቢዩ ኢሳይያስም ዙፋኑን እንደሚሸከሙ በምዕ ፴፯፥፲፮ ላይ “አቤቱ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ ሆይ አንተ ብቻኽን የምድር መንግሥታት ኹሉ አምላክ ነኽ ሰማይንና ምድርን ፈጥረኻል” በማለት ሲናገር፤ ነቢዩ ሕዝቅኤልም በፍርሀት ኹነው ሱራፌል ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳት) ዙፋኑን እንደተሸከሙ ኾኖ አይቷል (ሕዝ ፲፥፩-፳፪፤ ፲፩፥፳፪)፡፡ “የሚሸከሙት” ሲባል ግን በጸጋ የሚያድርባቸው፣ የሚቀድሱት፣ ዙፋኑን ተሸክመው ይታያሉና እንዲኽ ተባለ እንጂ “ይጸውር ድደ ወይነብር ጠፈረ ኲሉ እኁዝ ውስተ እራኁ ወአጽናፈ ዓለም በእዴሁ” ማለት (በጠፈር ተቀምጦ መሠረትን ይሸከማል፤ ኹሉ በመኻል እጁ የተያዘ የዓለም ዳርቾችም በእጁ ያሉ) እንዲለው የሚሸከማቸውስ ርሱ ነው፡፡ጌታችን እሳታውያን በኾኑ በኪሩቤል ዠርባ ላይ ተቀምጦ በአንድነት በሦስትነት እንደሚቀደስ ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ያስተምራሉ ዳዊትም “በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ በነፋስም ክንፍ በረረ” (መዝ ፲፰፥፲) በማለት ሲገልጽ፤ ዳግመኛም በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀምጦ የሚመሰገነው የእግዚአብሔር ልጅ የእስራኤል ዘነፍስ ጠባቂ ሊቀ ኖሎት ተገልጾ እንዲያድናቸው “ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ” በማለት የናፍቆት ልመናን ይለምን ነበር (መዝ ፸፱፥፩)፡፡ዮሐንስም በራእዩ ላይ በፍርሀት ኹነው ዙፋኑን ስለሚሸከሙት ስለ አርባእቱ እንስሳ ሲገልጽ “በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ፤ በዙፋኑም መኻከል በዙፋኑም ዙሪያ በፊትና በኋላ ዐይኖች የመሏቸው አራት እንስሶች ነበሩ፤ ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፤ ኹለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፤ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፤ አራተኛውም እንስሳ የሚበርረውን ንስር ይመስላል፤ አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ስድስት ክንፎች አሏቸው በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዐይኖች መልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ኹሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም” በማለት የኪሩቤልን የማያቋርጥ ምስጋናቸውን ተናግሯል (ራእ ፬፥፮‐፯)፡፡
ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ የሥነ ፍጥረት ነገር ተገልጾለት በጻፈው መጽሐፍ ላይ “ወለዳግም ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ ኪሩቤል ካህናተ ቅዳሴ ወውዳሴ እምታሕተ ሐቌሆሙ አሐዱ ወእምላዕለ ሐቌሆሙ አርባዕቱ እለ ግሉፋን በአዕይንት” ብሎ እንደገለጸው ኹለተኛውን አመስጋኞች የኾኑት ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ኪሩቤል ሲላቸው ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ሲፈጥራቸው ዐይናቸው ብዙ ነው፤ ይኽም ኀላፍያትን መጻእያትን በማወቃቸው ይተረጐማል፤ አለቃቸው ኪሩብ ሲኾን የሰው መልክና የአንበሳ መልክ ያለው ነው፡፡ ሦስተኛውን ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ሱራፌል ሲላቸው የእነዚኽ አለቃቸው የንስር መልክና የእንስሳ መልክ ያለው ሲኾን ሱራፊ ሲባል ሲፈጥራቸውም ስድስት ስድስት ክንፍ አድርጎ ፈጥሯቸዋል (ሕዝ ፩፥፬‐፲፩)
ሊቁ ኤጲፋንዮስም የሥነ ፍጥረትን ነገር በሚናገረው መጽሐፉ ላይ አኗኗራቸውን በጥልቀት ሲተነትነው “ወነሥአ እግዚአብሔር እምሰራዊተ ኪሩቤል ክልኤተ አርእስተ ዘውእቶሙ ገጸ ሰብእ ወገጸ አንበሳ ወዓዲ ነሥአ እግዚአብሔር እምሰራዊተ ሱራፌል ክልኤተ ክልኤተ አርእስተ ዘውእቶሙ ገጸ ንስር ወገጸ እንስሳ ወለክኦሙ መልዕልተ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት በማእዘንተ መርሕባ ለአርያም ወሰፍሐ ዲበ ዘባናቲሆሙ ሰማየ ዘሕብሩ በረድ” ይላል ከነገደ ኪሩቤል ኹለት ገጸ ሰብእ እና ገጸ አንበሳን ከሱራፌል ኹለት ገጸ ንስርና ገጸ እንስሳን አንሥቶ ከኢየሩሳሌም ሰማያዊት በላይ ከሰማይ ውዱድ በታች አቁሞ በነርሱ ላይ ሰማይ ውዱድን እንደ መረሻት ጫነባቸው፤ በላይም ሕብሩ በረድ የመሰለውን ዙፋን እንደ ሠረገላ ጭኖባቸዋል፤ እነዚኽንም በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በደቡብ በአራቱ መኣዝን ዠርባቸውን ወደ ውስጥ ፊታቸውን ወደ ውጪ እያደረገ አቁሟቸዋል፤ ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለዚኽ ነገር በምዕ ፩፥፲፪ ላይ “እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይኼድ ነበር መንፈስም ወደሚኼድበት ኹሉ ይኼዱ ነበር፥ ሲኼዱም አይገላመጡም ነበር” በማለት እንደተናገረ ገጽ ለገጽ ሳይተያዩ ሥላሴ በፈቀዱት ፍኖት አንዱ በኼደበት ሦስቱ እየተከታተሉ ይኼዳሉ፡፡
እነዚኽንም እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል ገለጻ ፲፮ ሲኾኑ የቀሩት ከውስጥ ስለኾኑ ስለማይታዩ አራቱ ግን ብቅ ብቅ ብለው ስለሚታዩ ዮሐንስ አራት ብሏቸዋል እንጂ እንደ ሕዝቅኤል ገጻቸው ፲፮ ነው፡፡ ሊቁ “እምርእሶሙ እስከ ሐቌሆሙ አርባዕቱ ወእምሐቌሆሙ እስከ እግሮሙ አሐዱ ከመ ርእየተ እለ ቄጥሩ ዘውእቱ ዖፍ ዘይነብር በሀገረ ፋርስ” እንዲላቸው፤ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በመጽሐፈ ድጓው ላይ “ከመ ርእየተ እለቄጥሩ ገጸ በገጽ ኢይትናጸሩ” ብሎ እንደገለጻቸው በፋርስ ሀገር የሚኖረው እለቄጥሩ የተባለውን ዎፍ ከወገቡ በታች አንድ ከወገቡ በላይ አራት እንደኾነ እነዚኽንም ከወገባቸው በታች አንድ ከወገባቸው በላይ አራት አድርጎ ፈጥሯቸዋል፤ የገጸ ሰብእ አቋቋሙ በምሥራቅ አተያዩ ወደ ምዕራብ ነው፤ የገጸ አንበሳ አቋቋሙ በምዕራብ አተያዩ ወደ ምሥራቅ፤ የገጸ ላሕም አቋቋሙ በሰሜን አተያዩ ወደ ደቡብ፤ የገጸ ንስር አቋቋሙ በደቡብ አተያዩ ወደ ሰሜን ሲኾን ገጽ ለገጽ አይተያዩም፡፡
የሰው መልክ ያለው ስለ ሰው ፍጥረት ይለምናል፤ የአንበሳ መልክ ያለው ስለ አራዊት ይለምናል፤ የንስር መልክ ያለው ስለ አዕዋፍ ይለምናል፤ የላም መልክ ያለው ስለ እንስሳ የሚለምን ሲኾን ከመላእክት ኹሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ዘንድ በባለሟልነት የቀረቡ ናቸው፡፡ በኢሳ ፮፥፩-፫ ላይ፡- “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረዥምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየኹት የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን መልቶት ነበር፤ ሱራፌልም ከርሱ በላይ ቆመው ነበር ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው በኹለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር በኹለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር በኹለቱም ክንፍ ይበር ነበር፤ አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ኹሉ ከክብሩ ተመልታለች እያለ ይጮኽ ነበር” ይላል ይኽ መሸፈናቸው ያድናቸዋል ቢሉ? ትእምርተ ፍርሀት ነው፤ ዛሬ በዚኽ ዓለም ሴቶችን ሕፃናትን እንመታችኋለን ባሏቸው ጊዜ እጃቸውን መጋረዳቸው የሚያድናቸው ኾኖ ሳይኾን ትእምርተ ፍርሀት እንደኾነ ኹሉ፡፡
አንድም በኹለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ፊትኽን ማየት አይቻለንም ሲሉ በኹለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ከፊትኽ መቆም አይቻለንም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ ያደርጋሉ አለ ትእምርተ ተልእኮ ነው፡፡ አንድም በኹለት ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው ባሕርይኽን መመርመር አይቻለንም ሲሉ፤ በኹለት ክንፋቸው እግራቸውን መሸፈናቸው ባሕርይኽን መረማመድ መተላለፍ አይቻለንም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወዲያ ወዲኽ ያደርጋሉ ከእእምሮ ወደ አእምሮ ለመፋለሳቸው፡፡አንድም ኹለት ክንፋቸውን ወደ ላይ አድርገው ይታያሉ አለ ወደላይ ቢወጡ ቢወጡ አትገኝም ሲሉ፤ ኹለት ክንፋቸውን ወደታች አድርገው ይታያሉ ወደታች ቢወርዱ ቢወርዱ አትገኝም ሲሉ፤ ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ ያደርጋሉ ወዲያና ወዲኽ ቢሉ አትገኝም ሲሉ፤አንድም ወደላይ መዘርጋት በሰማይ ምሉእ ነኽ ሲሉ ወደታች መዘርጋቸው በምድርም ምሉእ ነኽ ሲሉ፤ ወዲያና ወዲኽ መዘርጋታቸው በኹሉ ምሉእ ነኽ ማለታቸው ነው፤
አንድም ወደላይ መዘርጋት ትእምርተ ተመስጦ ወደታች መዘርጋት ትእምርተ ትሕትና፤ ወዲያና ወዲኽ ረብቦ መታየት ትእምርተ ተልእኮ ነው፤
በአጠቃላይ ኹለት ክንፋቸውን ወደላይ ኹለት ክንፋቸውን ወደታች ኹለት ክንፋቸውን ወዲያና ወዲኽ አድርገው ትእምርተ መስቀል መሥራታቸው በብሉይ ኪዳን ከኾነ እንዲኽ ባለ መስቀል ተሰቅለኽ ዓለምን ታድነዋለኽ ሲሉ በዘመነ ሐዲስ የኾነ እንደኾነ እንዲኽ ባለ ትእምርተ መስቀል ተሰቅለኽ ዓለምን አድነኸዋል ሲሉ ነው፡፡
የእነዚኽ አርባዕቱ እንስሳ ፊታቸው በርካታ ምስጢራትን ሲያመለክቱ ገጸ ሰብእ በማቴዎስ፤ ገጸ አንበሳ በማርቆስ፤ ገጸ ላሕም በሉቃስ፤ ገጸ ንስር በዮሐንስ ተመስሏል፤ በሌላ ምስጢር የሰው ገጽ ያለው የጌታን ሰው የመኾንን ነገር፤ የላም መልክ ያለው በቀራንዮ ላይ ደሙን ማፍሰሱ፤ የአንበሳው መልክ ያለው የጌታችንን ትንሣኤ፤ የንስር መልክ ያለው የጌታን ዕርገት እንደሚያመለክቱ መተርጒማን ይተነትኑታል፤ዐምደ ሃይማኖት አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም እጅግ ምጡቅ በኾነው ዕውቀቱ ዕጓለ አንበሳ የተባለው የወልድ የባሕርይ አባቱን አብን በአንበሳ ይመስለዋል፤ ሥጋን ተውሕዶ ፍጹም ሰው የኾነው ወልድን የሰው መልክ ባለው መስሎ ገልጾታል፡፡ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በወልድ ራስ ላይ ተቀምጦ የታየው መንፈስ ቅዱስን የንስር መልክ ባለው መስሎ አብራርቶ ጽፎታል፤ በቀንዱ የማይበራታ ላሕም ተብሎ የተመሰገነው የወልደ እግዚአብሔር ቅዱስ ሥጋው የሚፈትትባት፤ ክቡር ደሙ የሚቀዳባት በአራቱ ኪሩቤል አምሳል አራት መአዝን ያላት ቤተ ክርስቲያንን በገጸ ላሕም አምሳል ገልጦ አመስጥሮታል፡፡
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በድጓው ላይ፡-
“አርባእቱ እንስሳ በእንቲኣነ ጸልዩ
ኢይልክፈነ ለእሳት ዋዕዩ
እንስሳ አርባዕቱ መናብርቲሁ ለዋሕድ
መተንብላን ለኲሉ ትውልድ”
(አራቱ እንስሳ የሲኦል እሳት ግለቱ እንዳይነካን ስለ እኛ ጸልዩ፤ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አምላክ ዙፋኖቹ የኾኑ አራቱ እንስሳ ለትውልድ ኹሉ አማላጅ ናቸው) በማለት አንደተማፀነ እኛም የአምላካችንን ዙፋን የሚሸከሙ እነዚኽን ግሩማን መንፈሳውያን መላእክትን ከጌታችን ከአምላካችን ከክርስቶስ እንዲያማልዱን እንለምናለን፡፡
መጽሐፈ ሰዓታት ንባቡና ትርጓሜው ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ
የቤተክርስቲያን ትርጓሜ ምን ይላል ሊንኩን ይጫኑ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ